በጸሎት ወደ እግዚአብሔር እናገራለሁ፤ በቃሉ ደግሞ የእርሱን ድምፅ እሰማለሁ

መነሻ  ❖  ጽሑፎች
July 10, 2026  ❖  kira

አብዛኞቻችን ካደግንበት ሁኔታ አንጻር አንዳንድ ልምምዶች በቀላሉ አይለቁንም። ያደግንበት አካባቢ በቀጥታ “Charismatic” ባይሆንም እንኳ፣ አዕምሮአችን የተቀረጸውና የተገነባው በዚያው አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል። ይህ ሁኔታ በብዙ መንገድ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ጎድቶታል ብዬ አስባለሁ። አሁንም ሙሉ በሙሉ አልለቀቀኝም ብዬ ማሰቡ ያስፈራኛል፤ ምክንያቱም በጸሎት ሕይወት ላይ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ነው።

በጸሎት ሕይወቴ ውስጥ ከሚገጥሙኝ ተግዳሮቶች አንዱ “እግዚአብሔር እንደሰማኝ በምን አውቃለሁ?” የሚለው ጥያቄና ስጋት ነው። “ለምንድነው እንዲህ የሚሰማኝ? መጽሐፍ ቅዱስስ ከጸሎት በኋላ ምን እንዲሰማኝ ይነግረኛል? ወይም ምን እንድጠብቅ? እንደተሰማውሁ እንዲሰማኝ?” የሚሉ ጥያቄዎች በውስጤ ለምን የፈጠራለሁ?

ለነዚህ ጥያቄዎች አሁን መልስ አግኝቻለሁ። እግዚአብሔር ጸሎቴን መመለሱን የሚነግረኝ በጆሮዬ በሹክሹክታ “ሰምቼሃለሁ” በማለት ሳይሆን፣ የለመንኩትን በመስጠት፣ ወይም ደግሞ “ባለመስጠት” (ይህም ራሱ መልስ ነው) መሆኑን ተረድቻለሁ። ካልሆነም በመግቦቱ (Providence) ነገሩ የተለየ ዓላማ እንደነበረው ያሳየኛል። ይህ እስከሚሆን ድረስ ግን፣ ልመናዬ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እስከሆነ ድረስ መጸለዬን አላቆምም። እግዚአብሔር መልስ እስከሚሰጥ ወይም በመግቦቱ በሕይወቴ ውስጥ ያለውን መንፈሳዊ ትርጉም እስከሚያሳየኝ ድረስ በጸሎት እተጋለሁ።

በታድሶ ስነ-መለኮት (Reformed Theology) ትምህርት፣ ጸሎት ከጸጋ መንገዶች (Means of Grace) መካከል አንዱ ነው። በካቴኪዝም (Catechism) ውስጥ የተቀመጠበት ቅደም ተከተል በዘፈቀደ ሳይሆን የራሱ የሆነ ስነ-መለኮታዊ አንድምታ አለው። ለምሳሌ የሮሜ ወይም የኤፌሶን መጽሐፍ በጥንቃቄ በስርዓት (Systematically) እንደተቀመጡ ሁሉ፣ የትምህርተ መለኮት አደራደርም ትርጉም አለው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 1-3 ስለ ሰው ልጅ ውድቀትና አስከፊ የኃጢአት ሁኔታ እንጂ ስለ ደህንነት አያወራም። ስለ ክርስቶስ ማዳን ማውራት የሚጀምረው በምዕራፍ 3 አጋማሽ ላይ ነው። የዚህ አደራደር መልእክት ግልጽ ነው፦ “ሰው ያለበትን የኃጢአተኝነት ክፋት ካልተረዳ፣ የወንጌሉን የምስራች በእውነተኛ ትርጉሙ ሊረዳ አይችልም።” ይህ መርህ በሉተር “ትንሹ ካቴኪዝም” ውስጥም ይንጸባረቃል። አደራደሩ፦ ሕጉ (አሥርቱ ትእዛዛት)፣ ወንጌል (የሐዋርያት የሃይማኖት መግለጫ) እና ጸሎት (አባታችን ሆይ) በሚል የተቀመጠ ነው። በሕጉና በወንጌሉ በኩል እግዚአብሔር ወደ እኛ ይመጣል፤ እኛ ደግሞ በኃጢአት እውቅናና በወንጌል እምነት ወደ እግዚአብሔር በተከፈተልን በር በጸሎት ወደ እርሱ እንሄዳለን። ይህ መርህ ወሳኝ ነው፤ በሕጉና በወንጌሉ በኩል የእግዚአብሔርን ፈቃድ አውቄ እጸልያለሁ።

ጸልዬ ስጨርስ መልሱን በሁለት መንገድ እጠብቃለሁ፦
በቃሉ ብርሃን፦ የሕይወቴን መንገድ እመረምራለሁ።
በመግቦቱ (Providence)፦ በሕይወቴ የሚከናወኑትን ነገሮች ከቃሉ ስር ሆኜ እመለከታለሁ።

የእግዚአብሔርን ድምጽ ለመስማት የምጠብቀው በቃል ንባብና በስብከት ብቻ ነው። ካልሆነም ያነበብኩትን ቃል መንፈስ ቅዱስ በማንኛውም ጊዜ ወደ አዕምሮዬ አምጥቶ በትክክል እንዲገባኝ ሲያደርግ ፈቃዱን እረዳለሁ። በአጭሩ፤ ጸሎት እኔ ልመናዬን ወደ እግዚአብሔር የማቀርብበት “የማወራበት” ክፍል ሲሆን፣ በቅዱስ ቃሉ ደግሞ “ለመስማት” እቀመጣለሁ። ከዚያ ውጪ ድምጽ ፍለጋ በተሰወሩ መንገዶች አልሄድም።